የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው -አቶ አደም ፋራህ

 
መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ:: የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር "የኢትዮጵያን ይግዙ" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽን በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ በይፋ ተከፍቷል፡፡ ኤግዚብሽኑ ለሚቀጥሉት አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ገዥና ሻጭን ማገናኘት፣ በዘርፉ ያለውን አቅም ማሳየት እንዲሁም ንግድን በተመለከተ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ውይይቶች የሚደረጉበት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
 
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኢትዮጵያን ዕድገት ዘላቂ እና አስተማማኝ ለማድረግ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት መዘርጋት ይገባል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ስርዓት ተወዳዳሪ ማድረግ፣ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የንግዱ ማህበረሰብም በሃላፊነት በመስራት አገራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
በቅርቡ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ እየተፈጠሩ ካሉ ምቹ ሁኔታዎች መካከል መሆኑን ገልጸው ማሻሻያው የንግዱን ማህበረሰብ ጥያቄዎች የመለሰ ነው ብለዋል፡፡ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮችን በጥናት በመለየት እና የተሻሻሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ለንግዱ ዘርፍ መዘመንና መጠናከር ተግባራዊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ የንግድ ዘርፎችን መክፈት፣ ህጎችን ማሻሻል እና ዘመናዊ አሰራርን መዘርጋት በስፋት እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
 
ኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ ዲጂታል አሰራሮች ተግባራዊ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አቅቦትን ከማሻሻል አኳያም በተለይም 1 ሺህ 66 የእሁድ ገበያዎችን በማደራጀት ወደ ስራ መገባቱን አንስዋተል፡፡ በዛሬው ዕለትም የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነትና ትብብር የተንጸባረቀበት የወጭ ንግድ ቋሚ ማሳያ ማዕከል መከፈቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ይህም ለዘርፉ መሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
 

Contact Us

Petroleum and Energy Authority 

P.O.BOX 2554

Tel +251 

FAX +251

Email pea.info@pea.gov.et

Addis Ababa

Ethiopia

Address

Addis Ababa Kadco Group building #2 From 7th to 8th floor. Ethio china Friendship Avenue around Wello sefere.