ከነዳጅ አከፋፋይ ኩባኒያዎች ጋር በነዳጅ ግብይት ሂደቱ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ ፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን በነዳጅ ስርጭትና ግብይት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ሁሉም የነዳጅ አከፋፋይ ኩባኒያዎች በተገኙበት በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡
የምክክር መድረኩ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚንስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የሀገር ውስጥ ንግድ ላይሰንሲንግ ዘረፍ ሚኒስትር ዲኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር)፣የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ እስመለዓለም ምህረቱ እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሠሀርላ አብዱላሂ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ላይ የሀገር ውስጥ ንግድን ሕጋዊነት ለማስጠበቅና የተረጋጋ የንግድ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል በተለያዩ ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች የተገኘን ውጤት በነዳጅ ግብይት ሂደት ላይ ለማምጣት ትኩረት አድርጎ መስራት የሚኒስቴር መ/ቤቱ አቋም እንደሆነ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል ተገልጿል፡፡
በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በኩል እንደተነገረው በነዳጅ አቅርቦት ላይ እንደ ሀገር የሚገለጽ እጥረት አለመኖሩ፣ ሀገሪቱ በዓመት አራት ቢሊየን ዶላር መድባ ነዳጅ እንደምታስገባ ሆኖም በጅቡቲ ሆራይዘን የጭነት አቅም እንደ ችግር የሚገለፅ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ለችግሩ መባባስ ግን በዋነኝነት በነዳጅ ስርጭት ላይ በየደረጃው የሚስተዋሉ የስነምግባር ጥሰቶች ተጠቃሽ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ክልል ነዋሪዎች በተሰጠ መረጃ መሠረት የነዳጅ አቅርቦት ችግር ሳይኖር ማደያዎች ላይ የደረሰ ነዳጅ ምሽትን ተገን አድርጎ በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጣ ደርሰንበታል በማለት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተናግረዋል፡፡
በባለስልጣን መ/ቤቱ በኩል እንደተነገረው በአጠቃላይ በሀገሪቱ 560 ወረዳዎች ማደያ እንደሌላቸው የተነገረ ሲሆን ከዚህ በኋላ የሚገነቡ ነዳጅ ማደያዎች እነዚህን ቦታዎች ያማከለ ፣ በፀደቀው የነዳጅ ማደያወች ደረጃ መስፈርት መሠረት እንደሚሆን፣ የነዳጅ አቅርቦቱም ኢኮኖሚክ ዞን ተብለው በተለዩ 22 ከተሞች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚቀርብ መሆኑን በዋና ዳይሬክተሯ ሰሀርላ አብዱላሂ ተነግሯል፡፡ በነዳጅ አከፋፋይ ኩባኒያዎች በኩል ከገበያ ድርሻ ፍትሃዊነት፣ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ አሰጣጥ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ የስነምግባር ጥሰቶችና የቁጥጥር ሂደቱን በተመለከተ በተዘጋጁ የአሰራር ስርዓቶች አተገባባር ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ ሃሳቦች ተሰንዝረው ውይይት ተደርገባቸዋል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ በተሰጠ አቅጣጫ ኢንደስትሪው ስነምግባርና ሃላፊነትን ተላብሶ ጤናማ ውድድርን መሠረት አድርጎ ሊሠራ ይገባል የሚል አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡
|